Demokrati og diktatur // ዴሞክራሲና አምባገነንነት

ዴሞክራሲ- አብሮ መወሰን   

ዴሞክራሲ (ሕዝባዊ መንግስትም ተብሎም ይጠራል) ፣ የሃገሪቱ ህዝቦች፡ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ በሚተላለፉባቸው ጊዜያት፡ ጉዳዩ ላይ የመወሰን መብታቸው እሚከበርበትን ስርዓትን ለመግለጽ እምንጠቀምበት አጠራር ነው። ሕዝቦች ጉዳዪች ላይ የመወሰን መብታቸው ተግባራዊ የሚሆነው ደግሞ፡ በምርጫ ወቅት ላይ ድምጻቸውን በመስጠት ነው። ዴሞክራሲ፡ ልክ አንድ ሰው ብቻ ፈላጭ ቆራጭ የሚሆንበትን አምባገነናዊ ስርዓትን ጨምሮ ከሌሎች ስርዓቶች የተለየ ነው። ኖርዌይ ውስጥ ያለው የመንግስት ስርዓት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ነው። ይህም ማለት፡ ሁሉም ኖርዌይ ውስጥ እሚኖር ሰው፡ ማሕበረሰቡ እሚተዳደርበትን ደንብ በተመለከተ ሕግ በሚወጣበት ጊዜ አብሮ የመወሰን መብት አለው ማለት ነው። ህጻናትና ወጣቶችም፡ እነሱን እሚመለከቱ ጉዳዮች ሲነሱ፡ ሃሳባቸውን የመግለጽና የመሰማት መብት አላቸው።

ዴሞክራሲ እሚለው ቃል፡ «ዴሞስና» «ክራቲን» የተባሉ ሁለት የግሪክኛ ቃላቶችን የያዘ የሁለት ቃላት ውህደት ነው።  ዴሞስ ማለት ሕዝብ ማለት ሲሆን፣ ክራቲ ማለት ደግሞ መግዛት ወይ መምራት ማለት ነው። ሕዝባዊ መንግስት እሚለው ሃሳብ፡ የዛሬ 2500 አመት ገደማ በአቴና የተጸነሰ ሃሳብ ነው። ኖርዌይ ውስጥ፡ ሕብረተሰቡ እሚተዳደርበት ሕግ ላይ የተለያየ አመለካከት ያላቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ። የፓርላማ ምርጫ በሚኖርበት ጊዜ፡ ሁሉም 18 አመት የሞላቸው አዋቂዎች፡ በተሻለ የሚስማማቸውን የፖለቲካ ፓርቲ መምረጥ ይችላሉ።

Illustrasjon: Adobe Stock Mst3r

የመናገር ነጻነት

ዴሞክራሲ የመናገር ነጻነትን ያካተተ ነው። ይህም ማለት፡ ማንኛውም ሰው የተሰማውን መናገር ወይም መጻፍ የሚችል ሲሆን፡ የሚሰማውን በመናገሩ ወይም በመጻፉ አይቀጣም። ከህጻንነታችን ጀምሮ ፡ የምናስበውን፣ የሚሰማንን ወይም አመለካካታችንን ለመግለጽ እንለማመዳለን። በተመሳሳይም ሌሎች ሰዎች ከእኛ የተለየ ሃሳብ ሊኖራቸው እንደሚችል ማወቅና፡ የእነርሱንም ሃሳብ ማክበር እንደሚገባን መለማመድም አስፈላጊ ነው። ወደፊት ትልቅ በምትሆንበት ጊዜም፡ ሃሳቦችህ ከፍ ያለ ግምት የሚሰጣቸው ይሆናሉ።

ዴሞክራሲ- ነጻ ሚዲያ

ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባለበት ሃገር ውስጥ፡ የመገናኛ ብዙሃን፡ የተለያዩ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ ያግዛሉ። ኖርዌይ ውስጥ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች፡ በተለይም የምርጫ ቀን ሊደርስ ሲል፡ የተለያዩ ሚድያዎችን በመጠቀም ሃሳባቸውን ወደ ህዝብ ለማድረስ ይሞክራሉ።  ሕብረተሰቡ እንዴት መተዳደር እንዳለበት ፖለቲከኞቹ ሲወያዩ፡ በቲቪ፣ በጋዜጣ፣ በሬድዮና በኢንተርኔት መከታተል እንችላለን።

illustrasjon som viser trgning av en person som blir intervjuet
Illustrasjon: Adobe Stock MicroOne

አምባገነናዊ ስርዓት – አንድ ሰው ወይም በጣም ጥቂት ሰዎች ይወስናሉ

አንዳንድ ሃገራት በአምባገነናዊ ስርዓት ይመራሉ። በአምባገነናዊ ስርዓት እምትመራ ሃገር ውስጥ እሚወሰኑትን ውሳኔዎች በሙሉ የሚወስኑት አንድ ወይም በጣም ጥቂት የሆኑ፡ ስልጣን ያላቸው ሰዎች ናቸው። ባለስልጣኖቹን መቃወም አጥብቆ የተከለከለ ነው። ባለስልጣኖቹ እማይወዱትን ወይም እማይፈልጉትን ነገር መናገር ወይም መጻፍ ለእንግልትና ለእስር ሊዳርግ ይችላል። አንዳንዶችም በአመለካከታቸው ምክንያት ሊገደሉም ይችላሉ።.

ሃገሪቱን እሚመሩትን ሰዎች ቁጥር ብዛት ግምት ውስጥ በማስገባትና፣ ምን ያክል ነጻነት ሃገሪቱ ውስጥ እንዳለ በመገምገም ምን አይነት አምባገነናዊ ስርዓት ሃገሪቱ ውስጥ እንዳለ ለመግለጽ ይቻላል።

  • ሃገሪቱ  ውስጥ ያለው ስልጣን በሙሉ በአንድ ሰው እጅ ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ፡ በአምባገነን መሪ እምትመራ ሃገር ብለን እንገልጻታለን። ለምሳሌ የጀርመኑ አዶልፍ ሂትለር፣ የሶቭየቱ ጆሴፍ ስታሊን እና የስፔኑ ፍራንሲስኮ ፍራንኮ።
  • ሃገሪቱ ውስጥ ያለው ስልጣን በዛ ባሉ ወዳጅ በሆኑ ሰዎች መሃል ከሆነ፡ ስርዓቱ፡ ስርዓተ ጥቂት ወይም ኦሊጋርኪ ተብሎ ይገለጻል። ለምሳሌ፡ ወታደራዊ መንግስት እና አንድ ትልቅ የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ ያለበት አገር።

አምባገነናዊ ስርዓት – የመናገር መብት ያለው ጥቂት ነው።

በአምባገነናዊ ስርዓት በምትመራ ሃገር ውስጥ ያሉት የመገናኛ ብዙሃን ወይ የመንግስት ናቸው ወይም በመንግስት ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። በጋዜጣዎች፣ በሬድዮ እና በቲቪ እሚተላለፉት መልእክቶች በሙሉ፡ ባልስልጣናቱ እንዲተላለፍ የሚፈልጉት መልእክት ብቻ ነው። ሰዎች ሃሳባቸውን መናገርም ይሁን መጻፍ አይፈቀድላቸውም። ሰዎች እሚናገሩት ወይም እሚጽፉት ነገር ላይ እሚደረገው ቁጥጥር ሳንሱር ይባላል።